የማርቆስ ወንጌል
፩ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ። ፪-፬ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ። ፭ የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። ፮ ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር። ፯ ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል። ፰ እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር። ፱ በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። ፲ ወዲያውም ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና። የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ ፲፩ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ። ፲፪ ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው። ፲፫ በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ ከአራዊትም ጋር ነበረ፥ መላእክቱም አገለገሉት። ፲፬-፲፮ በገሊላ ባሕርም አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። ፲፯ ኢየሱስም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። ፲፰ ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ፲፱ ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ደግሞ በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አየ። ፳ ወዲያውም ጠራቸው አባታቸውንም ዘብዴዎስን ከሞያተኞቹ ጋር በታንኳ ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ። ፳፩ ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ። ፳፪ እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ። ፳፫ በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤ ፳፬ እርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ። ፳፭ ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ፳፮ ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ። ፳፯ ሁሉም። ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። ፳፰ ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ። ፳፱ ወዲያውም ከምኵራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገባ። ፴ የስምዖንም አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ነገሩት። ፴፩ ቀርቦም እጅዋን ይዞ አስነሣት ንዳዱም ወዲያው ለቀቃትና አገለገለቻቸው። ፴፪ ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ ፴፫ ከተማይቱም ሁላ በደጅ ተሰብስባ ነበር። ፴፬ በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፥ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፥ አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም። ፴፭ ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ። ፴፮ ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩትም ገሥግሠው ተከተሉት፥ ፴፯ ባገኙትም ጊዜ። ሁሉ ይፈልጉሃል አሉት። ፴፰ እርሱም። በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና አላቸው። ፴፱ በምኵራባቸውም እየሰበከ አጋንንትንም እያወጣ ወደ ገሊላ ሁሉ መጣ። ፵ ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ ተንበረከከና። ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው። ፵፩ ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው። ፵፪ በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀውና ነጻ። ፵፫ በብርቱም ተናግሮ ወዲያው አወጣው፤ ፵፬ ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ አለው። ፵፭ እርሱ ግን ሲወጣ ብዙ ሊሰብክና ነገሩን ሊያወራ ጀመረ፥ ስለዚህም ኢየሱስ ተገልጦ ወደ ከተማ መግባት ወደ ፊት ተሳነው፥ ነገር ግን በውጭ በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ከየስፍራውም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።