፳፪
፩ እናንተ ወንድሞች አባቶችም፥ አሁን ለእናንተ ነገሬን ስገልጥ ስሙኝ።
፪ በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም አለ።
፫ እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ
፬ ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ።
፭ እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር።
፮ ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤
፯ በምድርም ላይ ወድቄ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።
፰ እኔም መልሼ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አልሁ። እርሱም። አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አለኝ።
፱ ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አይተው ፈሩ፥ የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ ግን አልሰሙም።
፲ ጌታ ሆይ፥ ምን ላድርግ? አልሁት። ጌታም። ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድና ታደርገው ዘንድ ስለ ታዘዘው ሁሉን በዚያ ይነግሩሃል አለኝ።
፲፩ ከዚያ ብርሃንም ክብር የተነሣ ማየት ባይሆንልኝ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ።
፲፪ በዚያም የኖሩት አይሁድ ሁሉ የመሰከሩለት እንደ ሕጉም በጸሎት የተጋ ሐናንያ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።
፲፫ እርሱም ወደ እኔ መጥቶ በአጠገቤም ቆሞ። ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ አለኝ። እኔም ያን ጊዜውን ወደ እርሱ አየሁ።
፲፬ እርሱም አለኝ። የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል
፲፭ ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና።
፲፮ አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ።
፲፯ ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለሱ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፥
፲፰ እርሱም። ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት።
፲፱ እኔም። ጌታ ሆይ፥ በአንተ የሚያምኑትን በምኵራብ ሁሉ እኔ በወኅኒ አገባና እደበድብ እንደ ነበርሁ እነርሱ ያውቃሉ፤
፳ የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ።
፳፩ እርሱም። ሂድ፥ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁና አለኝ።
፳፪ እስከዚህም ቃል ድረስ ይሰሙት ነበር፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው። እንደዚህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ አይገባውምና አሉ።
፳፫ ሲጮኹና ልብሳቸውን ሲወረውሩ ትቢያንም ወደ ላይ ሲበትኑ፥
፳፬ የሻለቃው ወደ ሰፈሩ እንዲያገቡት አዘዘ፥ እንደዚህም የጮኹበትን ምክንያት ያውቅ ዘንድ። እየገረፋችሁ መርምሩት አላቸው።
፳፭ በጠፍርም በገተሩት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ። የሮሜን ሰው ያለ ፍርድ ትገርፉ ዘንድ ተፈቅዶላችኋልን? አለው።
፳፮ የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ። ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ ብሎ ነገረው።
፳፯ የሻለቃውም ቀርቦ። አንተ ሮማዊ ነህን? ንገረኝ አለው፤ እርሱም። አዎን አለ።
፳፰ የሻለቃውም መልሶ። እኔ ይህን ዜግነት በብዙ ገንዘብ አገኘሁት አለ። ጳውሎስም። እኔ ግን በእርስዋ ተወለድሁ አለ።
፳፱ ስለዚህም ሊመረምሩት ያሰቡት ከእርሱ ወዲያው ተለዩ፤ የሻለቃውም ደግሞ ሮማዊ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፥ አሳስሮት ነበርና።
፴ በማግሥቱም አይሁድ የከሰሱት በምን ምክንያት እንደ ሆነ እርግጡን ያውቅ ዘንድ አስቦ ፈታው፥ የካህናት አለቆችና ሸንጎውም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ፥ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።