፪
፩ ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ሁሉ እንዴት ያለ ትልቅ መጋደል እንዳለኝ ልታውቁ እወዳለሁና።  
፪ ልባቸው እንዲጸናና፥ በፍቅርም ተባብረው በማስተዋል ወደሚገኝበት ወደ መረዳት ባለ ጠግነት ሁሉ እንዲደርሱ የእግዚአብሔርንም ምሥጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ እጋደላለሁ።  
፫ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና።  
፬ ማንም በሚያባብል ቃል እንዳያስታችሁ ይህን እላለሁ።  
፭ በሥጋ ምንም እንኳ ብርቅ፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ሥርዓታችሁንም በክርስቶስም ያለውን የእምነታችሁን ጽናት እያየሁ ደስ ይለኛል።  
፮ እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ።  
፯ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ።  
፰ እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።  
፱ በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።  
፲ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።  
፲፩ የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ።  
፲፪ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።  
፲፫ እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ።  
፲፬ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።  
፲፭ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።  
፲፮ እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ።  
፲፯ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።  
፲፰ ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ።  
፲፱ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል።  
፳-፳፪ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና።  
፳፫ ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም።