፭
፩ በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።  
፪ እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ። ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም።  
፫ ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ።  
፬ በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።  
፭ እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና።  
፮ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።  
፯ በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ?  
፰ ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።  
፱-፲፩ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል።  
፲፪ የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ።  
፲፫ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ።  
፲፬ ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው።  
፲፭ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።  
፲፮ ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።  
፲፯ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።  
፲፰ በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም።  
፲፱ የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥  
፳ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥  
፳፩ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።  
፳፪ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።  
፳፫ እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።  
፳፬ የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።  
፳፭ በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።  
፳፮ እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።