፫
፩ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም።  
፪ ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።  
፫ በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።  
፬ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው።  
፭ እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም።  
፮ በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም።  
፯ ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው።  
፰ ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።  
፱ ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።  
፲ የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።  
፲፩ ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት። እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤  
፲፪ ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።  
፲፫ ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።  
፲፬ እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል።  
፲፭ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።  
፲፮ እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል።  
፲፯ ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?  
፲፰ ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።  
፲፱-፳፩ ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፥  
፳፪ ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን።  
፳፫ ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።  
፳፬ ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።