፫
፩ ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ።  
፪ መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።  
፫ ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።  
፬ ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው።  
፭ ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።  
፮ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።  
፯ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ።  
፰ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።  
፱ ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው።  
፲ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?  
፲፩ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም።  
፲፪ ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?  
፲፫ ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።  
፲፬-፲፮ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።  
፲፯ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።  
፲፰ በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።  
፲፱ ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።  
፳ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤  
፳፩ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።  
፳፪ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።  
፳፫ ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥  
፳፬ እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና።  
፳፭ ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ።  
፳፮ ወደ ዮሐንስም መጥተው። መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት።  
፳፯ ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው እንዳች ሊቀበል አይችልም።  
፳፰ እናንተ። እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን። ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ።  
፳፱ ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ።  
፴ እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል።  
፴፩ ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።  
፴፪ ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም።  
፴፫ ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ።  
፴፬ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና።  
፴፭ አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል።  
፴፮ በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።