፲፪
፩ በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።  
፪ በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤  
፫ ይዘውም ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት።  
፬ ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት አዋርደውም ሰደዱት።  
፭ ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፥ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ አንዳንዱንም ገደሉ።  
፮ የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ።  
፯ እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለው፥ ርስቱም ለኛ ይሆናል ተባባሉ።  
፰ ይዘውም ገደሉት፥ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት።  
፱ እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል ገበሬዎቹንም ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።  
፲-፲፪ ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ።  
፲፫ በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ።  
፲፬ መጥተውም። መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ? አሉት።  
፲፭ እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ። ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ አላቸው።  
፲፮ እነርሱም አመጡለት። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤ እነርሱም። የቄሣር ናት አሉት።  
፲፯ ኢየሱስም መልሶ። የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በእርሱም ተደነቁ።  
፲፰ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም አሉት።  
፲፱ መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን።  
፳ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤  
፳፩ ሁለተኛውም አገባት፥ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤  
፳፪ ሰባቱም አገቡአት፥ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች።  
፳፫ ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?  
፳፬ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን?  
፳፭ ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም።  
፳፮ ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር። እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን?  
፳፯ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።  
፳፰ ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ። ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው።  
፳፱ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥  
፴ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።  
፴፩ ሁለተኛይቱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።  
፴፪ ጻፊውም። መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤  
፴፫ በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው።  
፴፬ ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ። አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።  
፴፭ ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ። ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?  
፴፮ ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ።  
፴፯ ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር።  
፴፰-፵ የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።  
፵፩ ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤  
፵፪ አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች።  
፵፫ ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ። እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤  
፵፬ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው።