፭
፩ ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር መጡ።  
፪ ከታንኳይቱም በወጣ ጊዜ፥ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ከመቃብር ወጥቶ ወዲያው ተገናኘው፤  
፫ እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፥ በሰንሰለትም ስንኳ ማንም ሊያስረው በዚያን ጊዜ አይችልም ነበር፤  
፬ ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና ዳሩ ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፥ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም፤  
፭ ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን በመቃብርና በተራራ ሆኖ ይጮኽ ነበር ሰውነቱንም በድንጋይ ይቧጭር ነበር።  
፮ ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፥  
፯ በታላቅ ድምፅም እየጮኸ። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤  
፰ አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ ብሎት ነበርና።  
፱ ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው አለው፥  
፲ ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው።  
፲፩ በዚያም በተራራ ጥግ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበርና።  
፲፪ ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን ብለው ለመኑት።  
፲፫ ኢየሱስም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ገቡ፥ ሁለት ሺህም የሚያህል መንጋ ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና በባሕር ሰጠሙ።  
፲፬ እረኞቹም ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩ፤ ነገሩም ምን እንደ ሆነ ለማየት መጡ።  
፲፭ ወደ ኢየሱስም መጡ፥ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ።  
፲፮ ያዩት ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ እሪያዎቹ ተረኩላቸው።  
፲፯ ከአገራቸውም እንዲሄድላቸው ይለምኑት ጀመር።  
፲፰ ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው።  
፲፱ ኢየሱስም አልፈቀደለትም፥ ነገር ግን። ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው።  
፳ ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ።  
፳፩ ኢየሱስም ደግሞ በታንኳይቱ ወደ ማዶ ከተሻገረ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ በባሕርም አጠገብ ነበረ።  
፳፪ ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና።  
፳፫ ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው።  
፳፬ ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም።  
፳፭ ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥  
፳፮ ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤  
፳፯ የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች።  
፳፰ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና።  
፳፱ ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች።  
፴ ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ። ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ።  
፴፩ ደቀ መዛሙርቱም። ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ። ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት።  
፴፪ ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር።  
፴፫ ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው።  
፴፬ እርሱም። ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት።  
፴፭ እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት። ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት።  
፴፮ ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ። እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው።  
፴፯ ከጴጥሮስም ከያዕቆብም ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም።  
፴፰ ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤትም መጥቶ ሰዎች ሲንጫጩና ሲያለቅሱ ዋይታም ሲያበዙ አየ፤  
፴፱ ገብቶም። ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው።  
፵ በጣምም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናትም ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ።  
፵፩ የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው።  
፵፪ ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ።  
፵፫ ይህንም ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አዞአቸው። የምትበላውን ስጡአት አላቸው።