፰
፩ በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ።  
፪ ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤  
፫ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ አላቸው።  
፬ ደቀ መዛሙርቱም። በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት።  
፭ እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው፥ እነርሱም። ሰባት አሉት።  
፮ ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፥ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ለሕዝቡም አቀረቡ።  
፯ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ።  
፰ በሉም ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ።  
፱ የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ።  
፲ አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ።  
፲፩ ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር።  
፲፪ በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ።  
፲፫ ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ።  
፲፬ እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም።  
፲፭ እርሱም። ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው።  
፲፮ እርስ በርሳቸውም። እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ።  
፲፯ ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን?  
፲፰ ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን?  
፲፱ አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም። አሥራ ሁለት አሉት።  
፳ ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም። ሰባት አሉት።  
፳፩ ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው።  
፳፪ ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት።  
፳፫ ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፥ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት። አንዳች ታያለህን ብሎ ጠየቀው።  
፳፬ አሻቅቦም። ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ።  
፳፭ ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየና ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ።  
፳፮ ወደ ቤቱም ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው።  
፳፯ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም። ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው።  
፳፰ እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት።  
፳፱ እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም። አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት።  
፴ ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።  
፴፩ የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር።  
፴፪ ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።  
፴፫ እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለው።  
፴፬ ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።  
፴፭ ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል።  
፴፮ ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?  
፴፯ ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?  
፴፰ በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።