፲
፩ ወንድሞች ሆይ፥ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው።
፪ በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና።
፫ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም።
፬ የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።
፭ ሙሴ ከሕግ የሆነውን ጽድቅ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት እንዲኖር ጽፎአልና።
፮ ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል። በልብህ። ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤
፯ ወይም። በልብህ። ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው።
፰ ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው።
፱ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤
፲ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።
፲፩ መጽሐፍ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና።
፲፪ በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤
፲፫ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።
፲፬ እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?
፲፭ መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?
፲፮ ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና።
፲፯ እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።
፲፰ ዳሩ ግን። ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት። ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።
፲፱ ነገር ግን። እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ። እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ
፳ ብሎአል። ኢሳይያስም ደፍሮ። ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ አለ።
፳፩ ስለ እስራኤል ግን። ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።