፲፬
 ፩ ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ።   ፪ በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና፥ በመንፈስ ግን ምሥጢርን ይናገራል፤   ፫ ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል።   ፬ በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኅበሩን ያንጻል።   ፭ ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር፥ ትንቢትን ልትናገሩ ግን ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ፤ ማኅበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጐም በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።   ፮ አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ?   ፯ ነፍስ የሌለበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል?   ፰ ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?   ፱ እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና።   ፲ በዓለም ምናልባት ቁጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤   ፲፩ እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ፥ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል።   ፲፪ እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ።   ፲፫ ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ።   ፲፬ በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው።   ፲፭ እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ።   ፲፮ እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል?   ፲፯ አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም።   ፲፰ ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤   ፲፱ ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።   ፳ ወንድሞች ሆይ፥ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ።   ፳፩ ሌሎችን ልሳኖች በሚናገሩ ሰዎችና በሌላ አንደበት ለዚህ ሕዝብ እነግራቸዋለሁ፥ እንዲህም ቢሆን አይሰሙኝም ይላል ጌታ ተብሎ በሕግ ተጽፎአል።   ፳፪ እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም።   ፳፫ እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ። አብደዋል አይሉምን?   ፳፬ ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤   ፳፭ በልቡም የተሰወረ ይገለጣል እንዲሁም። እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።   ፳፮ እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን።   ፳፯ በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም፤   ፳፰ የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር።   ፳፱ ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤   ፴ በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል።   ፴፩ ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ።   ፴፪ የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ፤   ፴፫ እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።   ፴፬ ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና።   ፴፭ ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና፥ ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ።   ፴፮ ምን ነው? የእግዚአብሔር ቃል የወጣ ከእናንተ ነውን? ወይስ ወደ እናንተ ብቻ ደርሶአልን?   ፴፯ ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤   ፴፰ ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ።   ፴፱ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤   ፵ ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።