፲፮
 ፩ ለቅዱሳንም ገንዘብን ስለ ማዋጣት፥ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።   ፪ እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያን ጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ።   ፫ ስመጣም ማናቸውም ቢሆኑ የታመኑ የሚመስሉአችሁ ሰዎች ቸርነታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ ደብዳቤ ሰጥቼ እልካቸዋለሁ፤   ፬ እኔ ደግሞ ልሄድ የሚገባኝ ብሆን ከእኔ ጋር አብረው ይሄዳሉ።   ፭ በመቄዶንያም ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመቄዶንያ አድርጌ አልፋለሁና፤   ፮ እናንተም ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ምናልባት በእናንተ ዘንድ እቆይ ወይም እከርም ይሆናል።   ፯ አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጎበኛችሁ አልወድምና፤ ጌታ ቢፈቅደው የሆነውን ዘመን በእናንተ ዘንድ ልሰነብት ተስፋ አደርጋለሁና።   ፰ በኤፌሶን ግን እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ እሰነብታለሁ።   ፱ ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው።   ፲ ጢሞቴዎስም የመጣ እንደ ሆነ በእናንተ ዘንድ ያለ ፍርሃት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ ደግሞ የጌታን ሥራ ይሠራልና፤ እንግዲህ ማንም አይናቀው።   ፲፩ ነገር ግን ከወንድሞቹ ጋር እጠብቀዋለሁና ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ በሰላም በጉዞው እርዱት።   ፲፪ ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ግን ከወንድሞቹ ጋር ወደ እናንተ ሊሄድ እጅግ አድርጌ ለምኜው ነበር፤ ዛሬም ለመምጣት ከቶ ፈቃድ አልነበረውም፥ ሲመቸው ግን ይመጣል።   ፲፫ ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ።   ፲፬ በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።   ፲፭ ወንድሞች ሆይ፥ የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች የአካይያ በኩራት እንደ ሆኑ ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ፤   ፲፮ እንደ እነርሱ ላሉትና አብሮ ለሚሠራ ለሚደክምም ሁሉ እናንተም እንድትገዙ እለምናችኋለሁ።   ፲፯ በእስጢፋኖስና በፈርዶናጥስ በአካይቆስም መምጣት ደስ ይለኛል፥ እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን ፈጽመዋልና፤ መንፈሴንና መንፈሳችሁን አሳርፈዋልና።   ፲፰ እንግዲህ እንደነዚህ ያሉትን እወቁአቸው።   ፲፱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ በቤታቸው ካለች ቤተ ክርስቲያን ጋር በጌታ እጅግ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።   ፳ ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ።   ፳፩ እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌአለሁ።   ፳፪ ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና።   ፳፫ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።   ፳፬ ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሁላችሁ ጋር ነው። አሜን።