2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ   
 ፩
 ፩ በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚሆን የሕይወት ተስፋ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥   ፪ ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።   ፫ ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤   ፬ እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ።   ፭ በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ።   ፮ ስለዚህ ምክንያት፥ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፥ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ።   ፯ እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።   ፰ እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤   ፱ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥   ፲-፲፪ ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።   ፲፫ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤   ፲፬ መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።   ፲፭ በእስያ ያሉቱ ሁሉ ከእኔ ፈቀቅ እንዳሉ ታውቃለህ፥ ከእነርሱም ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስ ናቸው።   ፲፮ ጌታ ልሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፥ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤   ፲፯ በሰንሰለቴም አላፈረበትም፥ ነገር ግን በሮሜ ባደረ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ፤   ፲፰ በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም እንዴት እንዳገለገለኝ አንተ በደኅና ታውቃለህ።