የሐዋርያት ሥራ
፩
፩-፫ ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።
፬ ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን። ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤
፭ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ።
፮ እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት።
፯ እርሱም። አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤
፰ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።
፱ ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።
፲ እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤
፲፩ ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።
፲፪ በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
፲፫ በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።
፲፬ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።
፲፭ በዚህም ወራት ጴጥሮስ መቶ ሀያ በሚያህል በሰዎች ማኅበር አብረው በነበሩ በወንድሞቹ መካከል ተነሥቶ አለ።
፲፮ ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር፤
፲፯ ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበርና፥ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበርና።
፲፰ ይህም ሰው በዓመፅ ዋጋ መሬት ገዛ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ፤
፲፱ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህም ያ መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም የደም መሬት ማለት ነው።
፳ በመዝሙር መጽሐፍ። መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን የሚኖርባትም አይኑር፤ ደግሞም። ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት ተብሎ ተጽፎአልና።
፳፩-፳፫ ኢዮስጦስም የሚሉትን በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቆሙ።
፳፬-፳፮ ዕጣም ተጣጣሉላቸው፥ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።