፳፫
፩ ጳውሎስም ሸንጎውን ትኵር ብሎ ተመልክቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ አለ።
፪ ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ።
፫ በዚያን ጊዜ ጳውሎስ። አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፥ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን? አለው።
፬ በአጠገቡ የቆሙትም። የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን? አሉት።
፭ ጳውሎስም። ወንድሞች ሆይ፥ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር ተብሎ ተጽፎአልና አላቸው።
፮ ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ።
፯ ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም ተለያየ።
፰ ሰዱቃውያን። ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ።
፱ ታላቅ ጩኸትም ሆነ፥ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው። በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት ይሆን? ብለው ተከራከሩ።
፲ ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ።
፲፩ በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ። ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው።
፲፪ በጠባም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ።
፲፫ ይህንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤
፲፬ እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው። ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል።
፲፭ እንግዲህ አሁን እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ ስለ እርሱ አጥብቃችሁ እንደምትመረምሩ መስላችሁ ወደ እናንተ እንዲያወርደው ለሻለቃው አመልክቱት፤ እኛም ሳይቀርብ እንድንገድለው የተዘጋጀን ነን አሉአቸው።
፲፮ የጳውሎስ የእኅቱ ልጅ ግን ደባቸውን በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ ወደ ሰፈሩ ገባና ለጳውሎስ ነገረው።
፲፯ ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ። ይህን ብላቴና ወደ ሻለቃው ውሰድ፥ የሚያወራለት ነገር አለውና አለው።
፲፰ እርሱም ይዞት ወደ ሻለቃው ወሰደውና። ይህ ብላቴና የሚነግርህ ነገር ስላለው እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶ ወደ አንተ እንድወስደው ለመነኝ አለው።
፲፱ የሻለቃውም እጁን ይዞ ፈቀቅ አለና ለብቻው ሆኖ። የምታወራልኝ ነገር ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀው።
፳ እርሱም። አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል።
፳፩ እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ አለው።
፳፪ የሻለቃውም። ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው።
፳፫ ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ። ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ አላቸው።
፳፬ ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው።
፳፭ ደብዳቤም ጻፈ እንዲህ የሚል።
፳፮ ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን።
፳፯ ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፥ ሮማዊ እንደ ሆነ አውቄ ነበርና።
፳፰ የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤
፳፱ በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም።
፴ በዚህም ሰው አይሁድ ሴራ እንዲያደርጉበት ባመለከቱኝ ጊዜ ያን ጊዜውን ወደ አንተ ሰደድሁት፥ ከሳሾቹንም ደግሞ በፊትህ ይከሱት ዘንድ አዘዝኋቸው። ደኅና ሁን።
፴፩ ወታደሮቹም እንደ ታዘዙት ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት፤
፴፪ በነገውም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው ወደ ሰፈር ተመለሱ።
፴፫ እነዚያም ወደ ቂሣርያ ገብተው ደብዳቤውን ለአገረ ገዡ በሰጡ ጊዜ ጳውሎስን ደግሞ በፊቱ አቆሙት።
፴፬ ካነበበውም በኋላ የወዴት አውራጃ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ባወቀ ጊዜ።
፴፭ ከሳሾችህ ደግሞ ሲመጡ እሰማሃለሁ አለው፤ በሄሮድስም ግቢ ውስጥ ይጠብቁት ዘንድ አዘዘ።