፳፭
፩ ፊስጦስም ወደ አውራጃው ገብቶ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሣርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። ፪ የካህናቱ አለቆችና የአይሁድም ታላላቆች በጳውሎስ ላይ አመለከቱ፥ ፫ ጳውሎስንም ሲቃወም እንዲያደላላቸው እየለመኑ፥ በመንገድ ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ አስበው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያስመጣው ማለዱት። ፬ ፊስጦስ ግን ጳውሎስ በቂሳርያ እንዲጠበቅ እርሱም ራሱ ወደዚያ ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ እንዳለው መለሰላቸው፤ ፭ እንግዲህ በዚህ ሰው ክፋት ቢሆን ከእናንተ ዘንድ ያሉት ባለ ስልጣኖች ከእኔ ጋር ወርደው ይክሰሱት አላቸው። ፮ በእነርሱም ዘንድ ከስምንት ወይም ከአስር የማይበልጥ ቀን ተቀምጦ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በነገውም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን ያመጡት ዘንድ አዘዘ። ፯ በቀረበም ጊዜ ከኢየሩሳሌም የወረዱት አይሁድ ከበውት ቆሙ፥ ይረቱበትም ዘንድ የማይችሉትን ብዙና ከባድ ክስ አነሱበት፤ ፰ ጳውሎስም ሲምዋገት። የአይሁድን ህግ ቢሆን መቅደስንም ቢሆን ቄሳርንም ቢሆን አንዳች ስንኳ አልበደልሁም አለ። ፱ ፊስጦስ ግን አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን። ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር ከዚያው በፊቴ ትፋረድ ዘንድ ትወዳለህን? ብሎ መለሰለት። ፲ ጳውሎስ ግን። እፋረድበት ዘንድ በሚገባኝ በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተው ደግሞ ፈጽመህ እንደምታውቅ አይሁድን ምንም አልበደልሁም። ፲፩ እንግዲህ በድዬ ወይም ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ እንደ ሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ የሚከሱኝ ክስ ከንቱ እንደሆነ ግን ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠኝ ዘንድ ማንም አይችልም፤ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብዬአለሁ አለ። ፲፪ በዚያን ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብለሃል፤ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ ብሎ መለሰለት። ፲፫ ከጥቂት ቀንም በኋላ ንጉሡ አግሪጳ በርኒቄም ለፊስጦስ ሰላምታ እንዲያቀርቡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ። ፲፬ በዚያውም ብዙ ቀን ስለተቀመጡ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ገለጠ። ፊልክስ አስሮ የተወው አንድ ሰው በዚህ አለ፤ ፲፭ በኢየሩሳሌምም ሳለሁ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እፈርድበት ዘንድ እየለመኑ ስለ እርሱ አመለከቱኝ። ፲፮ እኔም። ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም ብዬ መለስሁላቸው። ፲፯ ስለዚህም በዚህ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ ሳልዘገይ በማግሥቱ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ ያንን ሰው ያመጡት ዘንድ አዘዝሁ። ፲፰ ከሳሾቹም በቆሙ ጊዜ እኔ ያሰብሁትን ክፉ ነገር ክስ ምንም አላመጡበትም፤ ፲፱ ነገር ግን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ጳውሎስ። ሕያው ነው ስለሚለው ስለ ሞተው ኢየሱስ ስለ ተባለው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ነበር። ፳ እኔም ይህን ነገር እንዴት እንድመረምር አመንትቼ። ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚህ ነገር ከዚያ ልትፋረድ ትወዳለህን? አልሁት። ፳፩ ጳውሎስ ግን አውግስጦስ ቄሣር እስኪቈርጥ ድረስ እንዲጠበቅ ይግባኝ ባለ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር እስክሰደው ድረስ ይጠበቅ ዘንድ አዘዝሁ። ፳፪ አግሪጳም ፊስጦስን። ያንንስ ሰው እኔ ዳግም እኮ እሰማው ዘንድ እወድ ነበር አለው። እርሱም። ነገ ትሰማዋለህ አለው። ፳፫ በነገውም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጥተው ከሻለቆችና ከከተማው ታላላቆች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስን አመጡት። ፳፬ ፊስጦስም አለ። አግሪጳ ንጉሥ ሆይ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው እየጮኹ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ በኢየሩሳሌም በዚህም ስለ እርሱ የለመኑኝን ይህን ሰው ታዩታላችሁ። ፳፭ እኔ ግን ሞት የሚገባውን ነገር እንዳላደረገ አስተዋልሁ፥ እርሱም ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ እሰደው ዘንድ ቈረጥሁ። ፳፮ ስለ እርሱም ወደ ጌታዬ የምጽፈው እርግጥ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር አገኝ ዘንድ በፊታችሁ ይልቁንም በፊትህ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ አመጣሁት፤ ፳፯ እስረኛ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት ደግሞ አለማመልከት ሞኝነት መስሎኛልና።