፩ ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። ፪ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። ፫ እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው። ፬ ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ። ወደ እኛ ተመልከት አለው። ፭ እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። ፮ ጴጥሮስ ግን። ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው። ፯ በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና፥ ፰ ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፥ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ። ፱ ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፤ ፲ መልካምም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ ስለ ምጽዋት ተቀምጦ የነበረው እርሱ እንደ ሆነ አወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መደነቅና መገረም ሞላባቸው። ፲፩ እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። ፲፪ ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ? ፲፫ የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። ፲፬ እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፥ ፲፭ የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፥ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን። ፲፮ በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፥ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው። ፲፯ አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ ፲፰ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው። ፲፱-፳፩ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና። ፳፪ ሙሴም ለአባቶች። ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት። ፳፫ ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ። ፳፬ ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ። ፳፭ እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም። በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። ፳፮ ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።