፯
፩ ሊቀ ካህናቱም። ይህ ነገር እንዲህ ነውን? አለው፤
፪ እርሱም እንዲህ አለ። ወንድሞችና አባቶች ሆይ፥ ስሙ። የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና።
፫ ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው።
፬ በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩባት ወደዚች አገር አወጣው።
፭ በዚችም የእግር ጫማ ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው።
፮ እግዚአብሔርም ዘሩ በሌላ አገር መጻተኞች እንዲሆኑ አራት መቶ ዓመትም ባሪያዎች እንዲያደርጉአቸው እንዲያስጨንቁአቸውም እንዲህ ተናገረ፤
፯ ደግሞም እግዚአብሔር። እንደ ባሪያዎች በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርድባቸዋለሁ፥ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ በዚህም ስፍራ ያመልኩኛል አለ።
፰ የመገረዝንም ኪዳን ሰጠው፤ እንዲሁም ይስሐቅን ወለደ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው ይስሐቅም ያዕቆብን ያዕቆብም አሥራ ሁለቱን የአባቶችን አለቆች።
፱ የአባቶችም አለቆች በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥
፲ ከመከራውም ሁሉ አወጣው፥ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፥ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይም ቢትወደድ አድርጎ ሾመው።
፲፩ በግብፅና በከነዓንም አገር ሁሉ ራብና ብዙ ጭንቅ መጣ፥ አባቶቻችንም ምግብን አላገኙም።
፲፪ ያዕቆብም በግብፅ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ በመጀመሪያ አባቶቻችንን ሰደዳቸው፤
፲፫ በሁለተኛውም ዮሴፍ ለወንድሞቹ ታወቀ፥ የዮሴፍም ትውልድ በፈርዖን ዘንድ ተገለጠ።
፲፬ ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ አስጠራ።
፲፭ ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ እርሱም ሞተ አባቶቻችንም፤
፲፮ ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በብር በገዛው መቃብር ቀበሩአቸው።
፲፯-፲፱ እርሱም ወገናችንን ተተንኵሎ ሕፃናትን በሕይወት እንዳይጠብቁ ወደ ውጭ ይጥሉ ዘንድ አድርጎ አባቶቻችንን አስጨነቀ።
፳ በዚያን ጊዜ ሙሴ ተወለደ በእግዚአብሔርም ፊት ያማረ ነበር፤ በአባቱ ቤትም ሦስት ወር አደገ፤
፳፩ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው።
፳፪ ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፥ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ።
፳፫ ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ።
፳፬ አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፥ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ።
፳፭ ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፥ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።
፳፮ በማግሥቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፥ ሊያስታርቃቸውም ወዶ። ሰዎች ሆይ፥ እናንተስ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ? አላቸው።
፳፯ ያም ባልንጀራውን የሚበድል ግን። አንተን በእኛ ላይ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው?
፳፰ ወይስ ትናንትና የግብፁን ሰው እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትወዳለህን? ብሎ ገፋው።
፳፱ ሙሴም ከዚህ ነገር የተነሣ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆች ወለደ።
፴ አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው።
፴፩-፴፫ ጌታም። የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ።
፴፬ በግብፅ ያሉትን የሕዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ፤ አሁንም ና፥ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ አለው።
፴፭ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው።
፴፮ ይህ ሰው በግብፅ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው።
፴፯ ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች። እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት ያላቸው ሙሴ ነው።
፴፰ ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤
፴፱ ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ፤
፵ አሮንንም። በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና አሉት።
፵፩ በዚያም ወራት ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፥ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው።
፵፪ እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በነቢያትም መጽሐፍ። እናንተ የእስራኤል ቤት፥ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን?
፵፫ ትሰግዱላቸውም ዘንድ የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል።
፵፬ እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤
፵፭ አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች።
፵፮ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ።
፵፯ ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት።
፵፰-፶፩ እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ።
፶፪-፶፬ ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።
፶፭ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና።
፶፮ እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ።
፶፯ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥
፶፰ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ።
፶፱ እስጢፋኖስም። ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር።
፷ ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።