፩ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ፪ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ ፫ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ፬ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ። ፭ እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና። ፮ እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን። ፯ ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። ፰ ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን። ፱ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። ፲ ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። ፲፩ ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። ፲፪ ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። ፲፫ ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። ፲፬ ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ፲፭ ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። ፲፮ የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? ፲፯ አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። ፲፰ በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? ፲፱ እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው እላለሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን? ፳ አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። ፳፩ የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ፳፪ ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? ፳፫ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። ፳፬ እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ። ፳፭ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤ ፳፮ ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነውና። ፳፯ ከማያምኑ ሰዎች አንዱም ቢጠራችሁ ልትሄዱም ብትወዱ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ። ፳፰ ማንም ግን። ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው ቢላችሁ ከዚያ ካስታወቃችሁና ከሕሊና የተነሣ አትብሉ፤ ፳፱ ስለ ባልንጀራህ ሕሊና እንጂ ስለ ገዛ ሕሊናህ አልናገርም። አርነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ Avረ ስለ ምንድር ነው? ፴ እኔም በጸጋ ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለ ምን እሰደባለሁ? ፴፩-፴፫ እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።