፲፭
፩ ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤
፪ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ።
፫ እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥
፬ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥
፭ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤
፮ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤
፯ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤
፰ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።
፱ እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤
፲ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።
፲፩ እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ።
፲፪ ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ። ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ?
፲፫ ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤
፲፬ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤
፲፭ ደግሞም። ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም።
፲፮ ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤
፲፯ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ።
፲፰ እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ።
፲፱ በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።
፳ አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።
፳፩ ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና።
፳፪ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።
፳፫ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤
፳፬ በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።
፳፭ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።
፳፮ የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤
፳፯ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው።
፳፰ ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።
፳፱ እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው?
፴ እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው?
፴፩ በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ።
፴፪ እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ።
፴፫ አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።
፴፬ በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ።
፴፭ ነገር ግን ሰው። ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል።
፴፮ አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤
፴፯ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤
፴፰ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል።
፴፱ ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው።
፵ ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው።
፵፩ የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና።
፵፪ የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤
፵፫ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤
፵፬ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ።
፵፭ እንዲሁ ደግሞ። ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።
፵፮ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም።
፵፯ የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።
፵፰ መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው።
፵፱ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።
፶ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።
፶፩-፶፫ ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።
፶፬ ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ። ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል።
፶፭ ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?
፶፮ የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤
፶፯ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
፶፰ ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።