፩ እኔም ራሴ ጳውሎስ፥ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ግን ብርቅ የምደፍራችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ፤ ፪ በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ፥ በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር እለምንችኋለሁ። ፫ በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ ፬ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ ፭ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ ፮ መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል። ፯ በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቁጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛ ደግሞ እንዲሁ ነን። ፰ ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም። ፱ በመልእክቶቼ የማስደነግጣችሁ አይምሰላችሁ። ፲ መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። ፲፩ እንዲሁ የሚል ይህን ይቁጠረው፤ በሩቅ ሳለን በመልእክታችን በኩል በቃል እንዳለን፥ በፊቱ ደግሞ ሳለን በሥራ እንዲሁ ነን። ፲፪ ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። ፲፫ እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም። ፲፬-፲፰ ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤