፪
፩ ወንድሞች ሆይ፥ ራሳችሁ ወደ እናንተ መግባታችን ከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና።
፪ ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን።
፫ ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኵሰት ወይም ከተንኰል አልነበረምና፤
፬ ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም።
፭ እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም፤
፮ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።
፯ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤
፰ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።
፱ ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን።
፲ በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤
፲፩-፲፫ ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።
፲፬ እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና።
፲፭ እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥
፲፮ ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል።
፲፯ እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤
፲፰ ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን።
፲፱ ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን?
፳ እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።