፲፫
፩-፫ ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ።
፬ መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።
፭ አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፥ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ። አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤
፮ ስለዚህ በድፍረት። ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን።
፯ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።
፰ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።
፱ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።
፲ መሠዊያ አለን፥ ከእርሱም ሊበሉ ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ መብት የላቸውም።
፲፩ ሊቀ ካህናት ስለ ኃጢአት ወደ ቅድስት የእንስሶችን ደም ያቀርባልና፤ ሥጋቸው ግን ከሰፈሩ ውጭ ይቃጠላል።
፲፪ ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ።
፲፫ እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ፤
፲፬ በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን።
፲፭ እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ በእርሱ እናቅርብለት።
፲፮ ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።
፲፯ ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።
፲፰ ጸልዩልን፤ በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፥ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና።
፲፱ ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ።
፳ በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥
፳፩ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
፳፪ ወንድሞች ሆይ፥ የምክርን ቃል እንድትታገሡ እመክራችኋለሁ፥ በጥቂት ቃል ጽፌላችኋለሁና።
፳፫ ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደ ተፈታ እወቁ፥ ቶሎ ብሎም ቢመጣ ከእርሱ ጋር አያችኋለሁ።
፳፬ ለዋኖቻችሁ ሁሉና ለቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከኢጣልያ የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
፳፭ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።