፯
፩ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤
፪ ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ አስራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው።
፫ አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።
፬ የአባቶች አለቃ አብርሃም ከዘረፋው የሚሻለውን አስራት የሰጠው ይህ ሰው እንዴት ትልቅ እንደ ነበረ እስኪ ተመልከቱ።
፭ ከሌዊ ልጆችም ክህነትን የሚቀበሉት ከህዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ፥ ከእነርሱ አሥራትን በሕግ እንዲያስወጡ ትእዛዝ አላቸው፤
፮ ትውልዱ ከእነርሱ የማይቈጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል።
፯ ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው።
፰ በዚህስ የሚሞቱ ሰዎች አሥራትን ያስወጣሉ፥ በዚያ ግን የሚያስወጣ በሕይወት እንዲኖር የተመሰከረለት እርሱ ነው።
፱ ይህንም ለማለት ሲፈቀድ፥ አሥራትን የሚያስወጣ ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል፤
፲ መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበረና።
፲፩ እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል?
፲፪ ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ የግድ ነውና።
፲፫ ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም፤
፲፬ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና፥ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳ ስለ ክህነት አልተናገረም።
፲፭-፲፯ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ይመሰክራልና።
፲፰-፳፪ እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።
፳፫ እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤
፳፬ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤
፳፭ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።
፳፮ ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤
፳፯ እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።
፳፰ ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።