፩ ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። ፪ የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ ፫ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ። አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም። አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ፬ ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? ፭ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? ፮ እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? ፯ የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? ፰ ነገር ግን መጽሐፍ። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ፱ ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል። ፲ ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ። አትግደል ብሎአልና፤ ፲፩ ባታመነዝርም፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግን ተላላፊ ሆነሃል። ፲፪ በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ። ፲፫ ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል። ፲፬ ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ፲፭ ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ፲፮ ከእናንተ አንዱም። በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? ፲፯ እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። ፲፰ ነገር ግን አንድ ሰው። አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። ፲፱ እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። ፳ አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? ፳፩ አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? ፳፪ እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? ፳፫ መጽሐፍም። አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ፳፬ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። ፳፭ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ፳፮ ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።