፲፪
፩ ከፋሲካም በፊት በስድስተኛው ቀን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ። ፪ በዚያም እራት አደረጉለት፤ ማርታም ታገለግል ነበር፤ አልዓዛር ግን ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት አንዱ ነበረ። ፫ ማርያምም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጕርዋም እግሩን አበሰች፤ ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ። ፬ ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ። ፭ ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ። ፮ ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው። ፯ ኢየሱስም። ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት፤ ፰ ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም አለ። ፱ ከአይሁድም ብዙ ሕዝብ በዚያ እንደ ነበረ አውቀው መጡ፥ ከሙታንም ያስነሣውን አልዓዛርን ደግሞ እንዲያዩ ነበረ እንጂ ስለ ኢየሱስ ብቻ አይደለም። ፲ የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፥ ፲፩ ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሣ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና። ፲፪ በማግሥቱ ወደ በዓሉ መጥተው የነበሩ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ፥ ፲፫ የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ ጮኹ። ፲፬-፲፮ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው። ፲፯ አልዓዛርንም ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ሲያስነሣው ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ይመሰክሩለት ነበር። ፲፰ ስለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ይህን ምልክት እንዳደረገ ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። ፲፱ ሰለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው። አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል ተባባሉ። ፳ በበዓሉም ሊሰግዱ ከወጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ ፳፩ እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው። ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት። ፳፪ ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። ፳፫ ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። ፳፬ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ፳፭ ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። ፳፮ የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። ፳፯ አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። ፳፰ አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም። አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። ፳፱ በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ። ነጐድጓድ ነው አሉ፤ ሌሎች። መልአክ ተናገረው አሉ። ፴ ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም። ፴፩ አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ ፴፪ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ። ፴፫ በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ። ፴፬ እንግዲህ ሕዝቡ። እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል፤ አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው? ብለው መለሱለት። ፴፭ ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። ፴፮ የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው። ፴፯-፵፩ ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ። ፵፪ ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ ፵፫ ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ፵፬ ኢየሱስም ጮኸ፥ እንዲህም አለ። በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ ፵፭ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። ፵፮ በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ፵፯ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። ፵፰ የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። ፵፱ እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። ፶ ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።