፩ ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር። ፪ የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ፫ እንግዲህ ወንድሞቹ። ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ፬ ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ አሉት። ፭ ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና። ፮ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ፯ ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል። ፰ እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም። ፱ ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ፲ ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። ፲፩ አይሁድም። እርሱ ወዴት ነው? እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። ፲፪ በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም። ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን። አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር። ፲፫ ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። ፲፬ አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። ፲፭ አይሁድም። ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር። ፲፮ ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፲፯ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። ፲፰ ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም። ፲፱ ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ፳ ሕዝቡ መለሱና። ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል? አሉት። ፳፩ ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ። ፳፪ ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። ፳፫ የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? ፳፬ ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ። ፳፭ እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ። ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? ፳፮ እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን? ፳፯ ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም። ፳፰ እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር። እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ ፳፱ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ ብሎ ጮኸ። ፴ ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። ፴፩ ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና። ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን? አሉ። ፴፪ ፈሪሳውያንም ሕዝቡ ሰለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጕሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ። ፴፫ ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ። ፴፬ ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ። ፴፭ እንግዲህ አይሁድ። እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሊሄድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን? ፴፮ እርሱ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው? ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ፴፯ ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ። ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። ፴፰ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ፴፱ ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና። ፵ ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ። ይህ በእውነት ነቢዩ ነው አሉ፤ ፵፩ ሌሎች። ይህ ክርስቶስ ነው አሉ፤ ሌሎች ግን። ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? ፵፪ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን? አሉ። ፵፫ እንግዲህ ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ ፵፬ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ወደዱ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም። ፵፭ ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነዚያም። ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው? አሉአቸው። ፵፮ ሎሌዎቹ። እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ። ፵፯ እንግዲህ ፈሪሳውያን። እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ፵፰ ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ፵፱ ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው ብለው መለሱላቸው። ፶ ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ። ፶፩ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። ፶፪ እነርሱም መለሱና። አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። ፶፫ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።