፩ ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ። ፪ ደቀ መዛሙርቱም። መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት። ፫ ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ። የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። ፬ ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። ፭ በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ። ፮ ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና። ፯ ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ። ፰ ጐረቤቶቹም ቀድሞም ሲለምን አይተውት የነበሩ። ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረ አይደለምን? አሉ። ፱ ሌሎች። እርሱ ነው አሉ፤ ሌሎች። አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ አሉ፤ እርሱ። እኔ ነኝ አለ። ፲ ታድያ። ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ? አሉት። ፲፩ እርሱ መልሶ። ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ አይኖቼን ቀባና። ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ አለ። ፲፪ ያ ሰው ወዴት ነው? አሉት። አላውቅም አለ። ፲፫ በፊት ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ፲፬ ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። ፲፭ ስለዚህ ፈሪሳውያን ደግሞ እንዴት እንዳየ እንደ ገና ጠየቁት። እርሱም። ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ ታጠብሁም አያለሁም አላቸው። ፲፮ ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ። ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም አሉ። ሌሎች ግን። ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል? አሉ። ፲፯ በመካከላቸውም መለያየት ሆነ። ከዚህም የተነሣ ዕውሩን። አንተ ዓይኖችህን ስለ ከፈተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ደግሞ አሉት። እርሱም። ነቢይ ነው አለ። ፲፰ አይሁድ የዚያን ያየውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕውር እንደ ነበረ እንዳየም ስለ እርሱ አላመኑም፥ ፲፱ እነርሱንም። እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል? ብለው ጠየቁአቸው። ፳ ወላጆቹም መልሰው። ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ አናውቃለን፤ ፳፩ ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል አሉ። ፳፪ ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፤ እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና። ፳፫ ስለዚህ ወላጆቹ። ሙሉ ሰው ነው፥ ጠይቁት አሉ። ፳፬ ስለዚህ ዕውር የነበረውን ሰው ሁለተኛ ጠርተው። እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን አሉት። ፳፭ እርሱም መልሶ። ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ አለ። ፳፮ ደግመውም። ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ? አሉት። ፳፯ እርሱም መልሶ። አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን? አላቸው። ፳፰ ተሳድበውም። አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ ፳፱ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት። ፴ ሰውዬው መለሰ እንዲህም አላቸው። ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፥ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። ፴፩ እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን። ፴፪ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ ፴፫ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር። ፴፬ መልሰው። አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን? አሉት። ወደ ውጭም አወጡት። ፴፭ ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም። አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው። ፴፮ እርሱም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ። ፴፯ ኢየሱስም። አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው። ፴፰ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም። ፴፱ ኢየሱስም። የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ አለ። ፵ ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሰምተው። እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን? አሉት። ፵፩ ኢየሱስም አላቸው። ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን። እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።