፲፩
፩ እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። ፪ አላቸውም። ስትጸልዩ እንዲህ በሉ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ ፫ የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ ፬ ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና፤ ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን። ፭ እንዲህም አላቸው። ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ። ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥ ፮ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን? ፯ ያም ከውስጥ መልሶ። አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን? ፰ እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል። ፱ እኔም እላችኋለሁ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፍትላችሁማል። ፲ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። ፲፩ አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ፲፪ ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? ፲፫ እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው? ፲፬ ዲዳውንም ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣ በኋላ ዲዳው ተናገረ ሕዝቡም ተደነቁ፤ ፲፭ ነገር ግን ከእነርሱ አንዳንዱ። በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ። ፲፮ ሌሎችም ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይፈልጉ ነበር። ፲፯ እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው። እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል። ፲፰ እኔ አጋንንትን በብዔል ዜቡል እንዳወጣ ትላላችሁና ሰይጣን ደግሞ እርስ በርሱ ከተለያየ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? ፲፱ እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። ፳ እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። ፳፩ ኃይለኛ ሰው ጋሻና ጦር ይዞ የራሱን ግቢ ቢጠብቅ፥ ያለው ገንዘቡ በሰላም ይሆናል፤ ፳፪ ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ መጥቶ ሲያሸንፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን ጋሻና ጦር ይወስድበታል ምርኮውንም ያካፍላል። ፳፫ ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። ፳፬ ርኵስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍትን እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ ባያገኝም። ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ፳፭ ሲመጣም ተጠርጎ አጊጦም ያገኘዋል። ፳፮ ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሌሎችን ሰባት አጋንንት ከእርሱ ጋር ይይዛል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ፳፯ ይህንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ። የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው። ፳፰ እርሱ ግን። አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ። ፳፱ ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር። ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ምልክት ይፈልጋል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ፴ ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። ፴፩ ንግሥተ አዜብ በፍርድ ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። ፴፪ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ፴፫ መብራትንም አብርቶ በስውር ወይም በእንቅብ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። ፴፬ የሰውነትህ መብራት ዓይንህ ናት። ዓይንህ ጤናማ በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ታማሚ በሆነች ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ የጨለመ ይሆናል። ፴፭ እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተመልከት። ፴፮ እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ የጨለማ ቍራጭ የሌለበት ብሩህ ቢሆን፥ መብራት በደመቀ ብርሃን እንደሚያበራልህ በጭራሽ ብሩህ ይሆናል። ፴፯ ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ። ፴፰ ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ ባየው ጊዜ ፈሪሳዊው ተደነቀ። ፴፱ ጌታም እንዲህ አለው። አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል ፵ እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን? ፵፩ ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። ፵፪ ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ፥ ወዮላችሁ፤ ነገር ግን ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር። ፵፫ እናንተ ፈሪሳውያን፥ በምኵራብ የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታ ስለምትወዱ፥ ወዮላችሁ። ፵፬ እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። ፵፭ ከሕግ አዋቂዎችም አንዱ መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ማለትህ እኛን ደግሞ መስደብህ ነው አለው። ፵፮ እርሱም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ ሕግ አዋቂዎች፥ አስቸጋሪ ሸክም ለሰዎች ስለምታሸክሙ፥ ራሳችሁም በአንዲት ጣታችሁ ስንኳ ሸክሙን ስለማትነኩት፥ ወዮላችሁ። ፵፯ አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፥ ወዮላችሁ። ፵፰ እንግዲህ ለአባቶቻችሁ ሥራ ትመሰክራላችሁ ትስማማላችሁም፤ እነርሱ ገድለዋቸዋልና፥ እናንተም መቃብራቸውን ትሠራላችሁ። ፵፱ ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች። ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ ያሳድዱማል፥ ፶ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም፥ ፶፩ ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፥ ከዚህ ትውልድ እንዲፈለግ አዎን እላችኋለሁ፥ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል። ፶፪-፶፬ እናንተ ሕግ አዋቂዎች፥ የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ፥ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ።