፲፰
፩ ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥ ፪ እንዲህ ሲል። በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። ፫ በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፥ ወደ እርሱም እየመጣች። ከባላጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር። ፬ አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ። ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥ ፭ ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ። ፮ ጌታም አለ። ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። ፯ እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ፰ እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን? ፱ ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ ፲ እንዲህ ሲል። ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። ፲፩ ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ። እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ ፲፪ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ። ፲፫ ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን። አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። ፲፬ እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል። ፲፭ እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው። ፲፮ ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ። ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። ፲፯ እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ። ፲፰ ከአለቆችም አንዱ። ቸር መምህር፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ፲፱ ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ፳ ትእዛዛቱን ታውቃለህ፥ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። ፳፩ እርሱም። ይህን ሁሉ ከሕፃንናቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለ። ፳፪ ኢየሱስም ይህን ሰምቶ። አንዲት ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። ፳፫ እርሱ ግን ይህን ሰምቶ እጅግ ባለ ጠጋ ነበርና ብዙ አዘነ። ፳፬ ኢየሱስም ብዙ እንዳዘነ አይቶ። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል። ፳፭ ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊገባ ይቀላል አለ። ፳፮ የሰሙትም። እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል? አሉ። ፳፯ እርሱ ግን። በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል አለ። ፳፰ ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ አለ። ፳፱ እርሱም። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥ ፴ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም አላቸው። ፴፩ አሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል። ፴፪ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፥ ይዘብቱበትማል ያንገላቱትማል ይተፉበትማል፤ ፴፫ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል። ፴፬ እነርሱም ከዚህ ነገር ምንም አላስተዋሉም፥ ይህም ቃል ተሰውሮባቸው ነበር፥ የተናገረውንም አላወቁም። ፴፭ ወደ ኢያሪኮም በቀረበ ጊዜ አንድ ዕውር እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር። ፴፮ ሕዝብም ሲያልፍ ሰምቶ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። ፴፯ እነርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል ብለው አወሩለት። ፴፰ እርሱም። የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ጮኸ። ፴፱ በስተ ፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። ፵ ኢየሱስም ቆሞ ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? ብሎ ጠየቀው። ፵፩ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አይ ዘንድ ነው አለው። ፵፪ ኢየሱስም። እይ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ፵፫ በዚያን ጊዜም አየ፥ እግዚአብሔንም እያከበረ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።