፩ ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ ፪ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ። ፫ ዲያብሎስም። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ። እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው። ፬ ኢየሱስም። ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት። ፭ ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ፮ ዲያብሎስም። ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ፯ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። ፰ ኢየሱስም መልሶ። ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው። ፱-፲፪ ኢየሱስም መልሶ። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል አለው። ፲፫ ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። ፲፬ ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። ፲፭ እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር። ፲፮ ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ። ፲፯-፳ መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። ፳፩ እርሱም። ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር። ፳፪ ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ። ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ይሉ ነበር። ፳፫ እርሱም። ያለ ጥርጥር ይህን ምሳሌ። ባለ መድኃኒት ሆይ፥ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግኸው የሰማነውን ሁሉ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ ትሉኛላችሁ አላቸው። ፳፬ እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ነቢይ በገዛ አገሩ ከቶ አይወደድም። ፳፭ ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፥ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ በምድር ሁሉ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ ፳፮ ኤልያስም በሲዶና አገር ወዳለች ወደ ሰራፕታ ወደ አንዲት መበለት እንጂ ከእነርሱ ወደ አንዲቱ አልተላከም። ፳፯ በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፥ ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልነጻም። ፳፰ በምኵራብም የነበሩ ሁሉ ይህን ሰምተው ቍጣ ሞላባቸው፥ ተነሥተውም ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፥ ፳፱ ይጥሉትም ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት፤ ፴ እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ። ፴፩ ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤ ፴፪ ቃሉ በሥልጣን ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ። ፴፫ በምኵራብም የርኵስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኾ። ፴፬ ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ። ፴፭ ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ። ፴፮ ሁሉንም መደነቅ ያዛቸው፥ እርስ በርሳቸውም። ይህ ቃል ምንድር ነው? በሥልጣንና በኃይል ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛልና፥ ይወጡማል ብለው ተነጋገሩ። ፴፯ ዝናም በዙሪያው ባለች አገር ወደ ስፍራው ሁሉ ስለ እርሱ ወጣ። ፴፰ በምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ንዳድ ታማ ነበር ስለ እርስዋም ለመኑት። ፴፱ በአጠገብዋም ቆሞ ንዳዱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ያንጊዜውንም ተነሥታ አገለገለቻቸው። ፵ ፀሐይም በገባ ጊዜ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ እርሱም በእያንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። ፵፩ አጋንንትም ደግሞ። አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ እየጮኹም ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ ገሠጻቸውም ክርስቶስም እንደ ሆነ አውቀውት ነበርና እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ፵፪ በጸባም ጊዜ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፥ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ወደዱ። ፵፫ እርሱ ግን። ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል አላቸው። ፵፬ በገሊላም ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።