፯
፩ ቃሉን ሁሉ በሕዝብ ጆሮዎች በጨረሰ ጊዜ ወደ ቅፍርናሆም ገባ።
፪ አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባሪያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር።
፫ ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው።
፬ እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው። ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤
፭ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት።
፮ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። አሁንም ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የመቶው አለቃ ወዳጆቹን ወደ እርሱ ላከ፤ አለውም። ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤
፯ ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል።
፰ እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፥ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፥ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል።
፱ ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ። እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው።
፲ የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ባሪያውን ባለ ጤና ሆኖ አገኙት።
፲፩ በነገውም ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ።
፲፪ ወደ ከተማይቱም በር በቀረበ ጊዜ፥ እነሆ፥ የሞተ ሰው ተሸክመው አወጡ፤ እርሱም ለእናቱ አንድ ልጅ ነበረ፥ እርስዋም መበለት ነበረች፥ ብዙም የከተማ ሕዝብ ከእርስዋ ጋር አብረው ነበሩ።
፲፫ ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና። አታልቅሽ አላት።
፲፬ ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፥ የተሸከሙትም ቆሙ፤ አለውም። አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ።
፲፭ የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፥ ለእናቱም ሰጣት።
፲፮ ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸውና። ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል፥ ደግሞ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐበኘ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
፲፯ ይህም ዝና ስለ እርሱ በይሁዳ ሁሉ በዙሪያውም ባለች አገር ሁሉ ወጣ።
፲፰ ደቀ መዛሙርቱም ለዮሐንስ እነዚህን ሁሉ አወሩ።
፲፱ ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ወደ እርሱ ጠርቶ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ።
፳ ሰዎቹም ወደ እርሱ መጥተው። መጥምቁ ዮሐንስ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ አንተ ላከን አሉት።
፳፩ በዚያች ሰዓት ከደዌና ከሥቃይ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፥ ለብዙ ዕውሮችም ማየትን ሰጠ።
፳፪ ኢየሱስም መልሶ። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፥ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ፥ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ፥ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤
፳፫ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው አላቸው።
፳፬ የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ?
፳፭ ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ።
፳፮ ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን።
፳፯ እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው።
፳፰ እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።
፳፱ የሰሙትም ሕዝብ ሁሉ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው እግዚአብሔርን አጸደቁ፤
፴ ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ስለ አልተጠመቁ የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው ጣሉ።
፴፩ እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን አስመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ?
፴፪ በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ። እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም ይላል።
፴፫ መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና። ጋኔን አለበት አላችሁት።
፴፬ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት።
፴፭ ጥበብም ለልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች።
፴፮ ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ።
፴፯ እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች።
፴፰ በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች።
፴፱ የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ። ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ።
፵ ኢየሱስም መልሶ። ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። እርሱም። መምህር ሆይ፥ ተናገር አለ።
፵፩ ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ።
፵፪ የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?
፵፫ ስምዖንም መልሶ። ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም። በእውነት ፈረድህ አለው።
፵፬ ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው። ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች።
፵፭ አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም።
፵፮ አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች።
፵፯ ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።
፵፰ እርስዋንም። ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት።
፵፱ ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው። ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው? ይሉ ጀመር።
፶ ሴቲቱንም። እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።