፲፫
፩ እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ አለው። ፪ ኢየሱስም መልሶ። እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው። ፫ በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም። ፬ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። ፭ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ፮ ብዙዎች። እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። ፯ ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ፰ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። ፱ እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። ፲ አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። ፲፩ ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። ፲፪ ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ ፲፫ በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ፲፬ ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥ ፲፭ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥ ፲፮ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። ፲፯ በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ፲፰ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ ፲፱ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። ፳ ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። ፳፩ በዚያን ጊዜም ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም። እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ፳፪ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። ፳፫ እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። ፳፬ በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ፳፭ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። ፳፮ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። ፳፯ በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። ፳፰ ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ ፳፱ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። ፴ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ፴፩ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። ፴፪ ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ፴፫ ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። ፴፬ ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። ፴፭ እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና ፴፮ ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። ፴፯ ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።