፩ ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፥ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ ፪ ሊከሱትም፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። ፫ እጁ የሰለለችውንም ሰው። ተነሥተህ ወደ መካከል ና አለው። ፬ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ። ፭ ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፥ ሰውየውንም። እጅህን ዘርጋ አለው። ፮ ዘረጋትም፥ እጁም ዳነች። ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ከሄሮድስ ወገን ጋር ተማከሩበት። ፯ ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ ፰ እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገው ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። ፱ ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ ፲ ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። ፲፩ ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ። ፲፪ እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው። ፲፫ ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ፲፬ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ፲፭ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ ፲፮ ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ ፲፯ የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ ፲፰ እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ ፲፱ አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን። ፳ ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ፳፩ ዘመዶቹም ሰምተው። አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ። ፳፪ ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም። ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። ፳፫ እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው። ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? ፳፬ መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ ፳፭ ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። ፳፮ ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። ፳፯ ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። ፳፰ እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ ፳፱ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም። ፴ ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና። ፴፩ እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። ፴፪ ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና። እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። ፴፫ መልሶም። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። ፴፬ በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና። እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። ፴፭ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።