፩ ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ፪ ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና። እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ፫ ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ፬ ኢየሱስም። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። ፭ በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ፮ ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። ፯ አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥ ፰ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። ፱ በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ። ፲ በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። ፲፩ ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። ፲፪ ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ ፲፫ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው። ፲፬ ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ። መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ። ፲፭ ሌሎችም። ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም። ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ። ፲፮ ሄሮድስ ግን ሰምቶ። እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ። ፲፯ ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ ፲፰ ዮሐንስ ሄሮድስን። የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና። ፲፱ ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤ ፳ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ ፳፩ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና ፳፪ የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን። የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ ፳፫ የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት። ፳፬ ወጥታም ለእናትዋ። ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች። ፳፭ ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። ፳፮ ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። ፳፯ ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ ፳፰ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። ፳፱ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት። ፴ ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። ፴፩ እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። ፴፪ በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ። ፴፫ ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ። ፴፬ ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። ፴፭ በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤ ፴፮ የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው አሉት። ፴፯ እርሱ ግን መልሶ። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት። ፴፰ እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ አላቸው። ባወቁም ጊዜ። አምስት፥ ሁለትም ዓሣ አሉት። ፴፱ ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው። ፵ መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ። ፵፩ አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ፵፪ ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ፵፫ ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ። ፵፬ እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ። ፵፭ ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ፵፮ ካሰናበታቸውም በኋላ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ፵፯ በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ። ፵፰ ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር። ፵፱ እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥ ፶ ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው። ፶፩ ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤ ፶፪ ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር። ፶፫ ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ። ፶፬ ከታንኳይቱም ሲወጡ ወዲያው አውቀውት ፶፭ በዚያች አገር ሁሉ ዙሪያ ሮጡና እርሱ እንዳለ ወደ ሰሙበት ስፍራ ሕመምተኞችን በአልጋ ላይ ያመጡ ጀመር። ፶፮ በገባበትም ስፍራ ሁሉ፥ መንደርም ከተማም ገጠርም ቢሆን፥ በገበያ ድውዮችን ያኖሩ ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።