፲፪
፩ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። ፪ ፈሪሳውያንም አይተው። እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት። ፫-፭ ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? ፮ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ፯ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር። ፰ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና። ፱ ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። ፲ እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት። ፲፩ እርሱ ግን። ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? ፲፪ እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው። ፲፫ ከዚያም በኋላ ሰውየውን። እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ፲፬ ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት። ፲፭ ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ ፲፮-፲፰ እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። ፲፱ አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፳ ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። ፳፩ አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ። ፳፪ ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው። ፳፫ ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና። እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን? አሉ። ፳፬ ፈሪሳውያን ግን ሰምተው። ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ። ፳፭ ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው። እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። ፳፮ ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? ፳፯ እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። ፳፰ እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። ፳፱ ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። ፴ ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። ፴፩ ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። ፴፪ በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። ፴፫ ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። ፴፬ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። ፴፭ መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። ፴፮ እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ፴፯ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ። ፴፰ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና። መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ። ፴፱ እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ፵ ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። ፵፩ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ፵፪ ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። ፵፫ ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም። ፵፬ በዚያን ጊዜም። ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ፵፭ ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል። ፵፮ ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። ፵፯ አንዱም። እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል አለው። ፵፰ እርሱ ግን ለነገረው መልሶ። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው። ፵፱ እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ። እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ ፶ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።