፲፬
፩ በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥ ፪ ለሎሌዎቹም። ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፥ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ። ፫ ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤ ፬ ዮሐንስ። እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና። ፭ ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው። ፮ ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ ፯ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። ፰ እርስዋም በእናትዋ ተመክራ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው። ፱ ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ፲ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። ፲፩ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፥ ወደ እናትዋም ወሰደችው። ፲፪ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፥ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት። ፲፫ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት። ፲፬ ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። ፲፭ በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት። ፲፮ ኢየሱስም። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው። ፲፯ እነርሱም። ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም አሉት። ፲፰ እርሱም። እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ አላቸው። ፲፱ ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፥ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ፳ ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። ፳፩ ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር። ፳፪ ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ፳፫ ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ። ፳፬ ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር። ፳፭ ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ። ፳፮ ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ። ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ። ፳፯ ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው። ፳፰ ጴጥሮስም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው። ፳፱ እርሱም። ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ። ፴ ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ፴፩ ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና። አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው። ፴፪ ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ። ፴፫ በታንኳይቱም የነበሩት። በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት። ፴፬ ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ። ፴፭ የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፥ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ ፴፮ የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።