፩ ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። ፪ እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። ፫-፭ ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። ፮ አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ፯ አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ። ፰ ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና። ፱ እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ፲ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ ፲፩ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ ፲፪ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ፲፫ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን። ፲፬ ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ፲፭ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። ፲፮ ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። ፲፯-፲፱ ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ፳ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ፳፩ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። ፳፪ የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ፳፫ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ! ፳፬ ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ፳፭ ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ፳፮ ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ፳፯ ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ፳፰ ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ ፳፱ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። ፴ እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? ፴፩ እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ፴፪ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ፴፫ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ፴፬ ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።