፪
፩ በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤
፪ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤
፫ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤
፬ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።
፭ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።
፮ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥
፯ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
፰ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።
፱ በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤
፲ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥
፲፩ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
፲፪ ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤
፲፫ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።
፲፬-፲፮ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል።
፲፯ ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤
፲፰ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ።
፲፱ ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ።
፳ እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤
፳፩ ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም።
፳፪ ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደ ሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ።
፳፫ እንግዲህ እንዴት እንደምሆን ባየሁ ጊዜ፥ እርሱን ቶሎ እንድልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤
፳፬ ራሴ ደግሞ ግን ፈጥኜ እንድመጣ በጌታ ታምኜአለሁ።
፳፭ ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤
፳፮ ሁላችሁን ይናፍቃልና፥ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል።
፳፯ በእውነት ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፥ ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይጨመርብኝ ለእኔ ደግሞ እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም።
፳፰ እንግዲህ እንደ ገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በብዙ ፍጥነት እልከዋለሁ።
፳፱ እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፥ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤
፴ በእኔ ዘንድ ካላችሁ አገልግሎት እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን እንዲፈጽም፥ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና።