፲፩
፩ እንግዲህ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? እላለሁ። አይደለም እኔ ደግሞ እስራኤላዊና ከአብርሃም ዘር ከብንያምም ወገን ነኝና። ፪ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝብ አልጣላቸውም። መጽሐፍ ስለ ኤልያስ በተጻፈው የሚለውን፥ በእግዚአብሔር ፊት እስራኤልን እንዴት እንደሚከስ፥ አታውቁምን? ፫ ጌታ ሆይ፥ ነቢያትህን ገደሉ መሠዊያዎችህንም አፈረሱ እኔም ብቻዬን ቀረሁ ነፍሴንም ይሹአታል። ፬ ነገር ግን አምላካዊ መልስ ምን አለው? ለበአል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ። ፭ እንደዚሁም በአሁን ዘመን ደግሞ በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ። ፮ በጸጋ ከሆነ ግን ከሥራ መሆኑ ቀርቶአል፤ ጸጋ ያለዚያ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል። ፯ እንግዲህ ምንድር ነው? እስራኤል የሚፈልጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ ፰ ሌሎቹም ደነዘዙ፤ እንዲሁም። ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ጆሮቻቸውም እንዳይሰሙ እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን እስከ ዛሬ ድረስ ሰጣቸው ተብሎ ተጽፎአል። ዳዊትም። ፱ ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ ማሰናከያም ፍዳም ይሁንባቸው፤ ፲ ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውንም ዘወትር አጉብጥ ብሎአል። ፲፩ እንግዲህ። የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን? እላለሁ። አይደለም፤ ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ፲፪ ዳሩ ግን በደላቸው ለዓለም ባለ ጠግነት መሸነፋቸውም ለአሕዛብ ባለ ጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን? ፲፫-፲፭ የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን? ፲፮ በኵራቱም ቅዱስ ከሆነ ብሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው። ፲፯ ነገር ግን ከቅርንጫፎች አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሀ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤ ፲፰ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን የምትሸከም አንተ አይደለህም። ፲፱ እንግዲህ። እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ ትል ይሆናል። ፳ መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። ፳፩ እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልሆነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና። ፳፪ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። ፳፫ እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። ፳፬ አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም? ፳፭ ወንድሞች ሆይ፥ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ምሥጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ ድንዛዜ በእስራኤል በአንዳንድ በኩል ሆነባቸው፤ ፳፮ እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል። ፳፯ ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው። ፳፰ በወንጌልስ በኩል ስለ እናንተ ጠላቶች ናቸው፥ በምርጫ በኩል ግን ስለ አባቶች ተወዳጆች ናቸው፤ ፳፱ እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና። ፴ እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር እንዳልታዘዛችሁ፥ አሁን ግን ከአለመታዘዛቸው የተነሣ ምሕረት እንዳገኛችሁ፥ ፴፩ እንዲሁ በተማራችሁበት ምሕረት እነርሱ ደግሞ ምሕረትን ያገኙ ዘንድ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም። ፴፪ እግዚአብሔር ሁሉን ይምር ዘንድ ሁሉን በአለመታዘዝ ዘግቶታልና። ፴፫ የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። ፴፬ የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ፴፭ ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ፴፮ ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።