፪
፩ ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና።
፪ እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን።
፫ አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን?
፬ ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?
፭ ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።
፮ እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤
፯ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤
፰ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።
፱ ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤
፲ ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው።
፲፩ እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።
፲፪ ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤
፲፫ በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና።
፲፬ ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤
፲፭ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።
፲፮ ይህም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እኔ በወንጌል እንዳስተማርሁ በሰው ዘንድ የተሰወረውን በሚፈርድበት ቀን ይሆናል።
፲፯ አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ፥
፲፰ ፈቃዱንም ብታውቅ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ፤
፲፱-፳፩ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን?
፳፪ አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን?
፳፫ በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን?
፳፬ በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ።
፳፭ ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፤ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለ መገረዝ ሆኖአል።
፳፮ እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን?
፳፯ ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል።
፳፰ በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤
፳፱ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።