፩-፫ በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። ፬ እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ ፭ አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን። ፮ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም። እነዚህ ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉምና፤ የአብርሃምም ዘር ስለሆኑ ሁላቸው ልጆች አይደሉም፥ ፯ ነገር ግን። በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ተባለ። ፰ ይህም፥ የተስፋ ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ እንጂ እነዚህ የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ማለት ነው። ፱ ይህ። በዚህ ጊዜ እመጣለሁ ለሳራም ልጅ ይሆንላታል የሚል የተስፋ ቃል ነውና። ፲ ይህ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ርብቃ ደግሞ ከአንዱ ከአባታችን ከይስሐቅ በፀነሰች ጊዜ፥ ፲፩ ልጆቹ ገና ሳይወለዱ፥ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ፥ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ፥ ፲፪ ለእርስዋ። ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተባለላት። ፲፫ ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ግን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ፲፬ እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ አለ ወይ? አይደለም። ፲፭ ለሙሴ። የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና። ፲፮ እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ። ፲፯ መጽሐፍ ፈርዖንን። ኃይሌን በአንተ አሳይ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ይነገር ዘንድ ለዚህ አስነሣሁህ ይላልና። ፲፰ እንግዲህ የሚወደውን ይምረዋል፥ የሚወደውንም እልከኛ ያደርገዋል። ፲፱ እንግዲህ ስለ ምን እስከ አሁን ድረስ ይነቅፋል? ፈቃዱንስ የሚቃወም ማን ነው? ትለኝ ይሆናል። ፳ ነገር ግን፥ አንተ ሰው ሆይ፥ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን። ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን? ፳፩ ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን? ፳፪-፳፬ የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፥ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን። ፳፭ እንዲሁ ደግሞ በሆሴዕ። ሕዝቤ ያልሆነውን ሕዝቤ ብዬ፥ ያልተወደደችውንም የተወደደችው ብዬ እጠራለሁ፤ ፳፮ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለላቸውም ስፍራ በዚያ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ ይላል። ፳፯-፳፱ ኢሳይያስም እንደዚሁ። ጌታ ፀባዖት ዘር ባላስቀረልን እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር ብሎ አስቀድሞ ተናገረ። ፴ እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልተከተሉት አሕዛብ ጽድቅን አገኙ፥ እርሱ ግን ከእምነት የሆነ ጽድቅ ነው፤ ፴፩-፴፫ እስራኤል ግን የጽድቅን ሕግ እየተከተሉ ወደ ሕግ አልደረሱም።