፲፬
፩ አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። ፪ እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ። ፫ በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም። ፬ ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። ፭ በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም። ፮ በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ ፯ በታላቅ ድምፅም። የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ። ፰ ሌላም ሁለተኛ መልአክ። አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቍጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች እያለ ተከተለው። ፱ ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው፥ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ። ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥ ፲ እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል። ፲፩ የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም። ፲፪ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው። ፲፫ ከሰማይም። ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ። አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ። ፲፬ አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው። ፲፭ ሌላ መልአክም ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው። የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፥ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ፲፮ በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው ምድርም ታጨደች። ፲፯ ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፥ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው። ፲፰ በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን። ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቍረጥ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ። ፲፱ መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፥ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቍጣ መጥመቂያ ጣለ። ፳ የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ።