፲፯
፩ ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ና በብዙም ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤
፪ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ።
፫ በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ።
፬ ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤
፭ በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም። ታላቂቱ ባቢሎን፥ የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት ተብሎ ተጻፈ።
፮ ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ።
፯ መልአኩም አለኝ። የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ።
፰ ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ።
፱ ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፥
፲ ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።
፲፩ የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው ከሰባቱም አንዱ ነው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል።
፲፪ ያየሃቸውም አስሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አስር ነገሥታት ናቸው፥ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ።
፲፫ እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፥ ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ።
፲፬ እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።
፲፭ አለኝም። ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው።
፲፮ ያየኃቸውም አስር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፥ ሥጋዋንም ይበላሉ፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል።
፲፯ እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና።
፲፰ ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።