፱
፩ አምስተኛውም መልአክ ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፥ የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው።
፪ የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ ፀሐይና አየርም በጕድጓዱ ጢስ ጨለሙ።
፫ ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፥ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው።
፬ የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተባለላቸው።
፭ አምስትም ወር ሊሣቅዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፤ እነርሱም የሚሣቅዩት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚሣቅይ ነው።
፮ በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ አያገኙትምም፥ ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል።
፯ የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ነው፥ በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፥ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፤
፰ የሴቶችን ጠጕር የሚመስል ጠጕር ነበራቸው፥ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፥
፱ የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፥ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምፅ ነበረ።
፲ እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው በጅራታቸውም መውጊያ አለ፥ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጐዱ ሥልጣን አላቸው።
፲፩ በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፥ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል።
፲፪ ፊተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል።
፲፫ ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ፥
፲፬ መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ። በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው።
፲፭ የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ።
፲፮ የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ፥ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ።
፲፯ ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፥ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ።
፲፰ ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ።
፲፱ የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፥ ራስም አላቸው በእርሱም ይጐዳሉ።
፳ በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤
፳፩ ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም።