፩ ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ፪ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ፫ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ፬ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ፭ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ፮-፰ ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ፱ ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም። ፲ አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ ፲፩ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ። ፲፪ በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ፲፫ ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፥ እያሳቱና እየሳቱ፥ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ። ፲፬ አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ፲፭-፲፯ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።