፳፮
፩ ኢየሱስም እነዚህን ቃሎች ሁሉ በፈጸመ ጊዜ፥  
፪ ለደቀ መዛሙርቱ። ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ፥ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል አለ።  
፫ በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥  
፬ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤  
፭ ነገር ግን። በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን አሉ።  
፮ ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥  
፯ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው።  
፰ ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቈጡና። ይህ ጥፋት ለምንድር ነው?  
፱ ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና አሉ።  
፲ ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው። መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ?  
፲፩ ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤  
፲፪ እርስዋ ይህን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች።  
፲፫ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።  
፲፬ በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ።  
፲፭ ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት።  
፲፮ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር።  
፲፯ በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት።  
፲፰ እርሱም። ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ። መምህር። ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ።  
፲፱ ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ።  
፳ በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።  
፳፩ ሲበሉም። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ።  
፳፪ እጅግም አዝነው እያንዳንዱ። ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር።  
፳፫ እርሱም መልሶ። ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው።  
፳፬ የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ።  
፳፭ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ። መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው።  
፳፮ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።  
፳፯ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤  
፳፰ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።  
፳፱ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም።  
፴ መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።  
፴፩ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤  
፴፪ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው።  
፴፫ ጴጥሮስም መልሶ። ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው።  
፴፬ ኢየሱስ። እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው።  
፴፭ ጴጥሮስ። ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ።  
፴፮ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ ደቀ መዛሙርቱንም። ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው።  
፴፯ ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር።  
፴፰ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው።  
፴፱ ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ። አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።  
፵ ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን። እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን?  
፵፩ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።  
፵፪ ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና። አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ።  
፵፫ ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው።  
፵፬ ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፥ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ።  
፵፭ ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል።  
፵፮ ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።  
፵፯ ይህንም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ።  
፵፰ አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።  
፵፱ ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ሳመው።  
፶ ኢየሱስም። ወዳጄ ሆይ፥ ለምን ነገር መጣህ? አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡ እጃቸውንም በኢየሱስ ላይ ጭነው ያዙት።  
፶፩ እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው።  
፶፪ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው። ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ።  
፶፫ ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?  
፶፬ እንዲህ ከሆነስ። እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?  
፶፭ በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም።  
፶፮ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው አለ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።  
፶፯ ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት።  
፶፰ ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ።  
፶፱ የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጐውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙም፤  
፷ ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙም።  
፷፩ በኋላም ሁለት ቀርበው። ይህ ሰው። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ ብሎአል አሉ።  
፷፪ ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ። እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን? አለው።  
፷፫ ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው።  
፷፬ ኢየሱስም። አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው።  
፷፭ በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ። ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል? አለ።  
፷፮ እነርሱም። ሞት ይገባዋል ብለው መለሱ።  
፷፯ በዚያን ጊዜ በፊቱ ተፉበት፤ ጐሰሙትም፥ ሌሎችም በጥፊ መትተው። ክርስቶስ ሆይ፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው?  
፷፰ ትንቢት ተናገርልን አሉ።  
፷፱ ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ። አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው።  
፸ እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ።  
፸፩ ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት። ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች።  
፸፪ ዳግመኛም ሲምል። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ካደ።  
፸፫ ጥቂትም ቈይተው በዚያ ቆመው የነበሩ ቀርበው ጴጥሮስን። አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አሉት።  
፸፬ በዚያን ጊዜ። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ሊራገምና ሊምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።  
፸፭ ጴጥሮስም። ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።