፳፯
፩ ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤  
፪ አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት።  
፫ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ።  
፬ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን። እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ።  
፭ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ።  
፮ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው። የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ።  
፯ ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት።  
፰ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ።  
፱ በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው። ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥  
፲ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ።  
፲፩ ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም። አንተ አልህ አለው።  
፲፪ የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም።  
፲፫ በዚያን ጊዜ ጲላጦስ። ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው።  
፲፬ ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም።  
፲፭ በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው።  
፲፮ በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው።  
፲፯ እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ። በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤  
፲፰ በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።  
፲፱ እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ። ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት።  
፳ የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ።  
፳፩ ገዢውም መልሶ። ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም። በርባንን አሉ።  
፳፪ ጲላጦስ። ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም። ይሰቀል አሉ።  
፳፫ ገዢውም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን። ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ።  
፳፬ ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ።  
፳፭ ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ።  
፳፮ በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ።  
፳፯ በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ አከማቹ።  
፳፰ ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥  
፳፱ ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤  
፴ ተፉበትም መቃውንም ይዘው ራሱን መቱት።  
፴፩ ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት።  
፴፪ ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።  
፴፫ ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥  
፴፬ በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም።  
፴፭ ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥  
፴፮ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር።  
፴፯ ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ።  
፴፰ በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ።  
፴፱ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና።  
፵ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ አሉት።  
፵፩ እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ።  
፵፪ ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን።  
፵፫ በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው።  
፵፬ ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር።  
፵፭ ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።  
፵፮ በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው።  
፵፯ በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ።  
፵፰ ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው።  
፵፱ ሌሎቹ ግን። ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ።  
፶ ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ።  
፶፩ እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤  
፶፪ መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤  
፶፫ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።  
፶፬ የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው። ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ።  
፶፭ ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤  
፶፮ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።  
፶፯ በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤  
፶፰ ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው።  
፶፱ ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥  
፷ ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ።  
፷፩ መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ።  
፷፪ በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና።  
፷፫ ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን።  
፷፬ እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት።  
፷፭ ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው።  
፷፮ እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።