፲
፩ በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።
፪ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ።
፫ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል። ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው።
፬ እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ። ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው። ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ።
፭ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ።
፮ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።
፯ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሎዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥
፰ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው።
፱ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ።
፲ ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤
፲፩ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤
፲፪ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት።
፲፫ ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።
፲፬ ጴጥሮስ ግን። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ።
፲፭ ደግሞም ሁለተኛ። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።
፲፮ ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ።
፲፯ ጴጥሮስም ስላየው ራእይ። ምን ይሆን? ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤
፲፰ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው። ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን? ብለው ይጠይቁ ነበር።
፲፱ ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ። እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤
፳ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ አለው።
፳፩ ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ። እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር ነው? አላቸው።
፳፪ እነርሱም። ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት።
፳፫ እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፥ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ።
፳፬ በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር።
፳፭ ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት።
፳፮ ጴጥሮስ ግን። ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ ብሎ አስነሣው።
፳፯ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፥ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ።
፳፰ አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤
፳፱ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ አላቸው።
፴ ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው። በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና።
፴፩ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ።
፴፪ እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ እንግድነት ተቀምጦአል አለኝ።
፴፫ ስለዚህ ያን ጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፥ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።
፴፬-፴፮ የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ።
፴፯ ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ።
፴፰ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤
፴፱ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።
፵ እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤
፵፩ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።
፵፪ ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን።
፵፫ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።
፵፬ ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።
፵፭ ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤
፵፮ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና።
፵፯ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ።
፵፰ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።