፲፩
፩ ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ።
፪ ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው።
፫ ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ አሉት።
፬ ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ።
፭ እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤
፮ ይህንም ትኵር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ።
፯ ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ።
፰ እኔም። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ ርኵስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና አልሁ።
፱ ሁለተኛም። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ።
፲ ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ እንደ ገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ።
፲፩ እነሆም፥ ያን ጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ።
፲፪ መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን።
፲፫ እርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና። ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤
፲፬ እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ነገር ይነግርሃል እንዳለው ነገረን።
፲፭ ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው።
፲፮ ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ።
፲፯ እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?
፲፰ ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና። እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።
፲፱ በእስጢፋኖስም ላይ በተደረገው መከራ የተበተኑት እስከ ፊንቄ እስከ ቆጵሮስም እስከ አንጾኪያም ድረስ ዞሩ፥ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድ ስንኳ አይናገሩም ነበር።
፳ ከእነርሱ ግን የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የነበሩት አንዳንዶቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው የጌታን የኢየሱስን ወንጌል እየሰበኩ ለግሪክ ሰዎች ተናገሩ።
፳፩ የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ።
፳፪ ወሬውም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ተሰማ፥ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት፤
፳፫ እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፥ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤
፳፬ ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ።
፳፭ በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ መጣ፤
፳፮ ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፥ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ።
፳፯ በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤
፳፰ ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ።
፳፱ ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ፤
፴ እንዲህም ደግሞ አደረጉ፥ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት።